እንኳን ለጌታችን ለመድሐኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የእርገት በዓል አደረሳችሁ !!!
- ጎዶልያስ
- Jun 6, 2019
- 5 min read
በዕርገቱ በዓል ምን እንማራለን?? ምንስ አገኘን?
ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋ.ስራ 1፡3 እንደተጻፈ ‹‹ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገርእየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ›› እያስተማረ የመሄጃው ቀን ሲደርስ እንዲህ አላቸው ፡፡ ‹‹እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።››ሉቃ 24፡49 ይሄን የመጨረሻ ኑዛዜ ቃል ከነገራቸው በኋላ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው ሲባርካቸውምከእነርሱ ተለየ >>ሉቃ 24፡50 እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎችሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድእንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው። >> ሐዋ 1፡9-11
የጌታ እርገት የምድር ስራውን ማጠናቀቁ ምልክት ነበር
ጌታ ገና አስቀድሞ በእለተ ትንሳኤው ለሐዋርያቱ በመግደላዊት ማርያም አማካኝነት መልዕክት ሲያስተላልፍ ‹‹ወደ ወንድሞቼሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት›› ዮሐ 20፡17 በዚህ ንግግሩ ጌታችን ሐዋርያቱ በእለተ ትንሳኤው ደስታ መመሰጥ ያለባቸው የሚያርግ ጌታ መመሆኑን በማወቅ እንጂ አብራቸው በምድር ከነሱ ጋር የሚኖር መስላቸው አስተሳሰባቸውን ምድራዊ እንዳያደርጉ ማሳሰቢያ መስጠቱ ነበር፡፡ ስለሆነም የጌታ ማረግ እርገቱንም መቀበል አስፈላጊው የእምነት አካል ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ለሐዋርያቱ ስለመንፈስ ቅዱስ ‹‹እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔእንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።›› ዮሐ 16፡7 አላቸው ፡፡ ሐዋርያት ጌታ አብራቸው በምድር ቢኖር ባይለያቸው ይወዱ ነበር ፡፡ ስለሆነም ጌታ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ እንዲመጣ እኔ መሄድ አለብኝ አላቸው ፡፡ እሱ ካልሄደ ለመንፈስ ቅዱስ የሚሆን ቦታ ስለማይበቃ ስፍራ መልቀቅ አለብኝ ማለቱ ሳይሆን እኔ በምድር የማልኖር፤ አርጌ በአባቴ ቀኝ መቀመጤን ሳትቀበሉ ይሄም ሳይሆን ፤ አሳባቹ ከምድራዊ መንፈስ ተላቆ ሰማያዊውን ህዮት መናፈቅ ሳያጀምር መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አትበቁም ማለቱ ነው፡፡ ስለሆነም እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና አላቸው፡፡ በአርባው የትንሳኤ በኋላ ቀናት ሐዋርያቱን ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ ስለቤ/ክ አገልግሎት ካስተማራቸው ቤ/ክንን እንዲመሩ ኃጢዓትን ይቅር እንዲሉ ካህን አርጎ ሾማቸው ፡፡ ‹‹ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስቅዱስን ተቀበሉ።ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።›› ዮሐ20 ፡23 ሁላችንም እንደምናውቀው በኋላ ሐዋርያት መንፈስቅዱስን የተቀበሉት በዕለተ በዓለ ኀምሳ /በበዓለ ጰራቅለጦስ/ እለት ነበር፡፡ ‹‹በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው።እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይተቀመጡባቸው።በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።››ሐዋ2፡1-4
ታዲያ ለምን አስቀድሞ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ አላቸው መንፈስቅዱስን ሐዋርያት ስንቴ ተቀበሉት ???
ሐዋርያት መንፈስቅዱስን የሚቀበሉት በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ቢሆንም ጌታ እፍ ብሎ በግርድፉ መንፈስቅዱስን ተቀበሉ ያለው ክህነትን ነበር ፡፡ እሱ ደግሞ የመንፈስ ጸጋ ስለሆነ መንፈስቅዱስን ተቀበሉ አለ፡፡ ሐዋርያት የተቀበሉት ክህነትን መሆኑን የምናረጋግጠው መንፈስቅዱስን ተቀበሉ ካለ በኋላ ‹‹ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸውተይዞባቸዋል ።›› ዮሐ20 ፡23 ማለቱን ስናስተውል ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ሲያርግ ‹‹እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔእልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።›› ሉቃ 24፡49 ባላለ ነበር ፡፡ ደቀመዛሙርቱ በአርባው ቀን ከጌታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከጌታ ስለመቅደስ ፡ ስለመስዋዕት፡ ስለ እጣን ስርዓት መማራቸውን እኛ እናምናለን ፡፡ለምን ቢሉ??? እንኳን ጌታ እውነተኛው መምህር ይቅርና የዚህ ዓም ትምህርት ቤት እንኳን ስለአሰራሩ ሳያስተምር አይሾምምና ፡፡ ነገር ግን ይሄን ከየት አገኛችሁት ቢባል መልሱ ከደረቁ የመጻፍ ንባብ ሳይሆን ከህዮታቸው አገኘነው መልሱ ነው፡፡
የጌታ እርገት በአባቱ ቀኝ በክብር የተቀመጠበት ቀን ፡፡
ጌታ ያረገው በክብር በዕልልታ በምስጋና ነው፡፡ ‹‹አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ ›› መዝ 47፡5 ‹‹እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።›› 1ኛ ጢሞ 3፡16 ‹‹ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበትይታያል፤ ›› ኤፌ1፡21
የጌታ እርገት አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ የተባለው ቃል የተገለጠበት ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባው ቃል ኪዳን ፍጻሜ አገኝቶ ይፋ የሆነበት ቀን ነው፡፡
ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበስራት ‹‹እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋንይሰጠዋል በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።››ሉቃ1፡32 ብሎ ነበር ፡፡ ያ ቀን የተፈጸመው በእለተ ዕርገቱ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥአለወው›› መዝ 110፡1 ‹‹እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም፥ እንዲህ ብሎ። ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ››መዝ 132፡11 > ራዕ 22፡16 በአብ ቀኝ ተቀምጦ ትንቢቱ ሁሉ ፍጻሜ አገኘ ፡፡ ‹‹እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ›› ዕብ 1፡3
የጌታ እርገት በሰማያዊ መቅደስ የእኛ መማራችን ይቅር የመባላችን ዋስትና ሆኖ በሰማያዊ መቅደስ ለሰዎች ኃጢአት ይቅር መባል ምልክት ሆነ
በለበሰው ስጋ በሰማያዊ ዘፋን በመቀመጡ ስጋ ይቅር መባሉ ብቻ አይደለም መክበሩ የታወቀበት ዕለት ነው፡፡ የዕርገቱ በዓል ሰው መዳኑ ብቻ ሳይሆን የለበሰውን ስጋ የተዋደው ጌታ በአብ ቀኝ በመቀመጡ ስጋ ከበረ ክብሩም ታየ፡፡ ‹‹ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።›› ዕብ 9፡24
የዕርገቱ ቀን ጌታ ወደ ሰማያዊ መቅደሱ የገባበት ዕለት ነው ፡፡
‹‹በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።››ዕብ 6፡20
የጌታ እርገት ለእኛ ቦታ ለማዘጋጀት ነበር
‹‹ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛእመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ›› ዮሐ 14፡1
የዕርገት ሕዮታዊ ትርጉም
በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ
ጌታ በሚያርግበት ጊዜ ሐዋርያቱን ‹‹እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይልእስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።›› ሉቃ 24፡49 አላቸው፡፡ በኢየሩሳሌም ቆዩ ማለት በከተማው የቁም እስረኛ ሆናችሁ ኑሩ ማለቱ ሳይሆን በመቅደስ ኢሩሳሌም ቆዩ ማለቱ ነበር ፡፡ ይሄም በመሆኑ ሐዋርያቱ ከዚህ የጌታ ትምህርት በኋላ ‹‹ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ›› ሉቃ 24፡53 ስለሆነም በቤተመቅደስ በጸሎት እየተጋ የሚቆይ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ይቀበላል ፡፡
በትህትና ያልወረደ ወደ ላይ አይወጣም
ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው?ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።>> ኢፌ 4፡9 ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ እንደክርስቶስ ካልወረዳችሁ ወደላይ አትወጡም ማለቱ ነው ፡፡ እውነት ነው አብዛኞቻችን የምናስበው መውጣትን እንጂ መውረድን አይደለም ስለሆነም ለመውጣት የሚያስብ ቀድሞ ወደታች በትህትና ይውረድ ፡፡ ጎበዝ ከክብሩ ስፍራ፤ ከደርቡ መውረድ አለብን ይህ ደግሞ ትህትና ነው ፡፡ እስመ በትህትና ረከበት ልዕልና አይደል የሚሉ አባቶች፡፡
ወደሰማይ ተኩር በሉ
‹‹እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ›› ሐዋ 1፡10 ሐዋርያቱ ከጌታ እርገት በኋላ ወደሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሁለት መላዕክት ተገልጠው አናገራቸው ፡፡
ቅዱስ አስጢፋኖስ ‹‹መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ›› አየ ሐዋ 7፡55 ሊቀዲያቆን ቀዳሜ ሰማያት አስጢፋኖስ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሰማይ ሲመለከት ጌታን በአብ ቀኝ አየው፡፡
‹‹ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ። ወደ እኛ ተመልከት አለውእርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ።ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው።›› ሐዋ 3፡4 ከሐዋርያቱ ትኩር ብሎ ማየት በኋላ ይሄ የኔቢጤ ወደ እነ ቅዱስ ጴጥሮስ መመልከት በመቻሉ ጤነኛ ሆኖ ሽባ እግሩ በርትቶ ተመላለሰ፡፡
‹‹ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና ›› ዕብ 11 ፡24-26
ቅዱስ ሙሴ ትኩር ብሎ ብድራቱን በማየቱ ዓለማዊ ተድላ ፍርኦናዊ ደስታ ንቆ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንደሆነ አስተዋለ ፡፡
ጎበዝ እኛስ ምንድነው ትኩር ብለን እየያን ያለው፡፡ ??
ጌታ ሲያርግ የአተኮሩ መላዕክት ተገለጡላቸው ፡፡ መንፈሳዊ መላዕክት የማይገለጡልን ወደሰማይ ስለማናተኩር ነው ፡፡
በሽተኛ ሆነን የቀረነው በቤተመቅደስ ደጅ እየመጣን እየዋልን በርትተን ያልተነሳነው የነጴጥሮስ ድምጽ ሰምተን ሰለማናተኩር ወደ እውነተኞቹ ጴጥሮሶች ስለማናይ ነው፡፡
እስጢፋኖስ ሲያተኩር ጌታን አየ፡፡ መከራን ቻለ ድንጋይ ለሚወረውሩበት ይቅርታ ማድረግ ብቻ አይደለም ክርስቶስን መስሎ ምህረትን ለመነ እኛ ይቅርታ የማናደርገው መከራ የማንችለው ጌታን ስለማናይ ትኩር ብለን ሰማያዊውን ነገር ስለማናስተውል ነው፡፡
ሙሴ የክርስቶስ ብድራቱን ትኩር ብሎ ቢያይ ግብፃዊነቱን ናቀ ዓለምን ጠላ ፡፡ስለ ክርስቶስ መነቀፍ ን መረጠ…… አኛም ስለክርስቶስ ብናስተውል ዓለምን እንጠላለን፡፡ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ መንፈሳዊ መከራን እንመርጣለን፡፡
ጌታ ያረገው ከምድር ስበት ሕግ ውጪ ነው እሱን የሚመስሉ የምድር ኃይል ያሸንፋሉ
ምድር ወደላይ የሚወጣውን ሁሉ ወደ ታች የሚስብ ጉልበት አላት ስለሆነም ወደላይ ለመውጣት የሳን የምድር ስበት ሕግ ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ ጌታ ከምድር ስበት ሕግ በላይ በመሆኑ አረገ ፡፡ እንደሱ ለማረግ የሚፈልግ ምድራዊ ጎታች ከሆነው ከዚህ ዓለም ፍላጎት፤ኃጢኣት ነጻ መሆን አለበት ፡፡
ጌታ ሲያርግ የተገለጡት ሁለቱ መላዕክት ‹‹የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው ›› ሐዋ 1፡11 የዕርገቱ ማጠናቀቂያ መልዕክት ጌታ ይመጣል ነው ፡፡ ምፅአቱን እናስብ ፡፡ ‹‹ይህን የሚመሰክር። አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።›› ራዕ 22፡20
አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ መዝ 47፡5
ተጻፈ
በዲያቆን ሳምሶን ኃ/ሚካኤል /ዘሆሳዕና በዓለወልድ//

Comments