top of page
Search

የሰኔ ጾም

  • Writer: ጎዶልያስ
    ጎዶልያስ
  • Jun 17, 2019
  • 3 min read

ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገር ሁሉ መከልከል ማለት ነው፡፡ ወይም ለሥጋ የሚመቸውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ጾም አለ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና አለው፡፡ ይልቁንም በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ ነበረው፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውኃ ለአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘዳ 34፥28/ በኃጢአታቸው ብዛት የመጣባቸው መዓት የሚመልሰው ቁጣውም የሚበረደው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ /ዮና 3፥5-10/፡ በአዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕል ሥጋዌው መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ /ማቴ 4፥21/ ጌታችን በሦስት በፍቅረ ንዋይና በትዕቢት የሚመጣበትን ጠላት ዲያብሎስ በጾም ድል እንድምንነሣው አሳየን፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር ጠላት ሰይጣንን በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ተናግሯል /ማቴ 17፥21/፡ ስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ /የሐዋ13፥3፤4፥25/ እነ ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ክብር ያገኙት በጾማና በጸሎት ፈጣሪያቸው ማልደው ነው /የሐዋ 10፥20/

ጾም እንኳን የጠበቅነውንና ያሰብነውን ቀርቶ ያላሰብነውንና ያልጠበቅነውን ፈጽሞም የማይገባንን ጸጋና ክብር የሚያሰጥ ነው፡ በሐዋርያት መሠረት ላይ የተመሠረተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጾም ሕግና ሥርዓት አላት እነዚህም የፈቃድና የአዋጅ አጽዋማት ይባላሉ፡፡ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ የሐዋርያት (የሰኔ) ፆም ነው፡፡

ይህም ጾም በሕዝብ ዘንድ የወታደር ጾም ይባላል፡፡ ለስብከተ ወንጌል ዘመቻ የተዘጋጀ በጾሙት ተምሣሌት በድሮ ዘመን ወታደሮች ለዘመቻ ሲነሱ ወይም ከዘመቻ ሲመለሱ በተሳተ በተገጸፈ ይቅር በለን በማለት ይጾሙት ነበር፡፡ ይህም ጾምየሚፈሰክበት ከሐምሌ 5 የማይለቅ ቢሆንም የሚጀመርበት ግን የተወሰነ ቀን የለውም በዚህም ምክንያት የጾሙ ዕለት ቁጥር ከፍና ዝቅ ይላል አንዳንድ ጊዜ ከአርባ ይበልጣል አንዳንድ ጊዜ ከ30 ያንሣል የ2008 ዓ.ም. ጾም ሰኔ 13 ገብቶ ለሦስት ሳምንት ይጾማል፡፡

📷

ሐዋርያት መቼ ጾሙ?

ቅዱሳን ሐዋርያት የአምላካቸውን የመምህሮቸዋል አርአያ ተከትለው እርሱ ወደ ማዳን ሥራው /ሕሙማነ ሥጋን በተዓምህራት/ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት ከማዳን አስቀድሞ የሥራውን መጀመሪያ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ 40 ቀን 40 ሌሊት እንደ ጾመና እንደጸለየ ሁሉ ቅዱሳን ሐዋርያትም አብነቱን ተከትለው ጾመዋል፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ዓለምን ዕጣ ተጣጥለው (ተከፈፍለው) ዞረው ከማስተማራቸው አስቀድመው የሥራቸው መጀመሪያን ጾምን አድርገዋል፡፡

ሐዋርያትም ይህንን ጾም እንደሚጾሙ ጌታችን አስቀድሞ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው በጠየቁት ጊዜ ተናግሮ ነበር፡፡ “እኛናፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀመዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለምንድን ነው? አሉት ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ሚዜዎችሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉ? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወስድበት ወራት ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ” /ማቴ 9፥15-16/፡፡

የሰኔ ጾም የቄስ ብቻ ነውን?

ይህ ጥያቄ ብዙ ሰዎች የሚነሣ ጥያቄ ነው ብዙ ምእመናን የሰኔን ጾም አይጾሙም ለመጾም የሚፈልጉትንም ሰዎች የቄስ ነው እያሉ ሲነቅፉ ይታያሉ ነገር ግን ይህ ጾም ከሰባቱ የአዋጅ ጾም አንዱ ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታቸንን ምሣሌ አድርገው የጾሙት እኛም እነርሱን አርአያ አድርገነው ልንጾመው የሚገባ የበረከት ጾም ነው፡፡ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ “ክርስቲያኖች ነን” ባዮች “ከመጾም ተቆጥበው ቀሳውስት ብቻ የሚጾሙት ነው!” ይላሉ ለራስ የከበደን ነገር በሌላው ላይ መጫን ተገቢ አይደለም ካላወቁ ለማወቅ መማር ዐውቆ ከማጥፍት መቆጠብ ተገቢ መሆኑን መዘንጋት አይገባም

እኛ ይህን ጾም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመካፈል፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን በመሆኑ ይህንን ዲያብሎስን ድል ማድረጊያ መሣሪያ አንጣለው ጾሙም ለመላው ክርስቲያን የተሰጠ እንጂ የቀሳውስት ብቻ አይደለም ለቄስና ለምእመናን ተብሎ በክህነት ደረጃ የተለየ ጾምም የለም፡፡

እንዴትና ከምን እንጹም?

የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ ከኃጢአት ቁራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ለአምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ የአልኮል መጠጦች ሥጋና ቅቤ ወተትና እንቁላል ማራቅ ተገቢ ነው፡፡ ሥጋዊ ጉልበትን በጾም የማድከም ቅብአት ካላቸው ምግቦች መከልከልም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር “ጉልበቶቼበጾም ደከሙ ሥጋዮም ቅቤ በማጣት ከሳ” ብሏል /108፥24/፡፡ ሠለስቱ ደቂቅና ነቢዩ ዳንኤልም የቤተ መንግሥቱን ሥጋና የጸሎት ምግብ ትተው በጥሬና በውኃ መቆየታቸው ተጽፏል /ት.ዳን 1፥8-21፣ት.ዳን10፥2/ ዋናው ነገር ጾም እንጂ መብል ወደ እግዚአብሔር አያቀረበንም ብንበላም የምናተርፈው ባንበላም የሚጎዳን ነገር የለም፡፡ /1ኛ ቆሮ8 ፥8/ ከአዳም ጀምሮ መብል ሲጥል እንጂ ሲያነሣ አላየንምና ጾሙን ከኃጢአት በመራቅ ለራስ ያስብነውን ለነዳያን በመስጠት፣ ጾም ከጸሎት ጋር ሲሆን ጸጋን እንደ ሐዋርያቱ ያሠጣልና በጸሎት በመትጋት በስግደት ወደ እግዚአብሔር በፍጹም ልብ በመመለስ ልንጾመው ይገባል፡፡

📷

ቅዱስ ኤፍሬም “ጾም የነፍስ ድግስ፣ ክብረ በዓል ነው” ብሎ ተናግሯል፡፡ ጾም ነፍስን ሐብታም ያደርጋታል፡፡ አዕምሮውን ንጹህ ከማድረጉም ባሻገር በጠላት ላይ መንፈሰ ጠንካራ ያደርጋል ጾም ጥሩ ሥነ-ምግባራትን የሚያዳብር መንፈሳዊ ሕይወት ነው፡፡ ይኸውም ንጽህናን፣ ትዕግስትን ድንግልናን፣ ደስታን ……ወዘተ በተጨማሪም የታላቁ ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደስ የሆነውን አካላትንን ለንጽህና ለእርሱ እንድናስገዛ ያደርገናል፡፡

ጾም ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ ያደርገናል፡፡ /ት.ኢዩ 2፥12/ “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በለቅሶና በዋይታወደ እኔ ተመለሱ!” ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበትን የልብ መነሳሳት እውነት ያደርግናል በጾማችን እግዚአብሔርን የምናደበት የቅድስና ሕይወት እንፈጥራለን ታላቁ ነቢዩ ኢሳይያስ በኃጢአቱ ተጸጽቶ የጾመው ጾም ለኃጢአቱ ሥርየት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርንም ክብር ለማየት አብቅቶታል /ት.ኢሳ6፥1/፡፡ በአጠቃላይ ጾም የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት ነው የአገልግሎትና የቅድስናችንም መጀመሪያ ሊሆን ይገባል፡፡

 
 
 

Commentaires


Post: Blog2_Post

©2019 by ጎዶልያስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መዝሙር. Proudly created with Wix.com

bottom of page