❤️✝️የእመቤታችን የልደት በዓል✝️❤️
- ጎዶልያስ
- Jun 6, 2019
- 3 min read

በቀደመው ዘመን በዘመነ ብሉይ “የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል” ይከበር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ይህ በዓል እስከ ጌታችን ዘመንም ይከበር ነበር፡፡ /ዮሐ 10፥22/ በሐዲስ ኪዳን እዉነተኛ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ለሆነችው እመቤታችን በስሟ በዓል ሊደረግላት ይገባል “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል” እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ 111፥7/
በተአምረ ማርያም ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሠላሳ ሦስት በዓላት አሏት፡፡ ከእነዚህ በዓላት ሁሉ አስበልጣ የምትወደው በዓለ ልደቷን እንደሆነ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ በተተረጎመው እመቤታችን በተለያዩ ሀገራት ያደረገቻችዉን ገቢረ ተአምራት በኢትዮጵያ ከተፈጸሙት ጋር አካቶ የያዘው ተአምረ ማርያም በዝርዝር ያስረዳል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱና ምሉዕነት የሌላቸው ታሪኮች በአዋልደ መጻሕፍት እንደሚሟሉ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ዳዊት የሚናገረው መጽሐፈ ዜና መዋዕል “የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ እንዲሁም በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ላይ ተጽፏል” /1ኛ ዜና 29፥29/
✝️✝️የእመቤታችን ታሪክ✝️✝️
የእመቤታችን ወላጆች በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ “ሃና” እና ኢያቄም /ዮአኪን በሚለው ስም የሚጠሩ ሲሆን ሃና በቤተልሔም ተወልዳ እንዳደገች ታሪክ ያስረዳል፡፡ በናዝሬት ገሊላ ለመሥዋዕት የሚሆኑ በጎች የሚያቀርብ እንዲሁም እረኛ የነበረውን ኢያቄምንም አግብታለች፡፡ ቅድስት ሃና ወደ ቤተ መቅደስ ስትሔድ አርጋብን አይታ ታለቅስ ነበር፡፡ ከብዙ ልመና በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያምን ግንቦት አንድ ቀን በደብረ ሊባኖስ ወልደዋል፡፡
ስለ ሃና መካንነት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው መባዕ ሲያቀርቡ ካህኑ ያልተቀበላቸዉ መሆኑን በብስራተ መልአክ ልጅ እንደሚወልዱ እንደተነገራቸው በእኛ ቤተ ክርስቲያን የሚተረከውና በሌሎች ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚነገረው ታሪክ ተመሳሳይ ነው፡፡
✝️✝️እመቤታችን የት ተወለደች?✝️✝️
እመቤታችን ስለተወለደችበት ስፍራ በዓለም የተለያዩ ሀሳቦች ይስተጋባሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በዶግማ አንድነት ባላቸው አኃት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በእንዲህ ዓይነት ታሪክ ነክ ጉዳዮች ላይ ልዩነት መኖራቸው የተለመደ ክስተት ነው፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሀሳቦች የሚያነሱ ሲሆን አንደኛው “ድንግል ማርያም ብስራተ መልአክ በሰማችበት ናዝሬት ተወልዳለች” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ “ከሦስተኛው ክ/ዘመን ወዲህ የማርያም መግቢያ ተብሎ በሚታወቀው ከኢየሩሳሌም የቅድስት ሃና የክሩሲድ ቤተ ክርስቲያን በታች ነዉ የተወለደችው” የሚል ነው፡፡
የግብጽ ስንክሳር የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ በናዝሬት ነው ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ስንክሳር ግን በቀደምትነታቸው ተጠብቀው የቆዩ ከመሆናቸው አንጻር ተአማኒነታቸው የጎላ መሆኑን ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡ ሊባኖስ ከገሊላ በስተ ሰሜንና ከፍንቄ በስተ ምስራቅ ይገኛል፡፡ “ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ” የሚለዉ ቃለ ትንቢት ምስጢርም የአመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸው የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ /መኃ 4፥7/
✝️✝️የልደታ ለማርያም በዓል መቼ ነው?✝️✝️
እንደተወለደችበት ሥፍራ የእመቤታችን የልደት ቀን እንዲሁ አወዛጋቢ ነው፡፡ በ 6ኛውና 7ኛው መቶ/ክ/ዘመን ነው የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች የተጻፉ ሲሆን Encyclopaedic of Christian antiquities ደግሞ በ431 ዓ/ም ከተካሄደውና ንስጥሮስ ከተወገዘበት ከጉባኤ ኤፌሶን በኋላ ነው ይላል፡፡ በዓለም ቅዱሳንን የሚያከብሩ አብያተ ክርስቲያናት የቅዱሳንን በዓለ እረፍታቸውን የሚያከብሩ ሲሆን ልደታቸው የሚከበረውም በሦስተኛ ደረጃ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስዮሐንስ፤ በሁለተኛ ደረጃ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ የአመቤታችን ልደት በምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ኬክ በመጋገር፡ የአመቤታችን ትንሽ ሀውልት በማቆም ዐሥር ሻማዎችን በማብራት ያከብራሉ፡፡
✝️✝️የድንግል ማርያም ልደት ለምን ይከበራል?✝️✝️
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አንደበት “በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” በማለት ተነግሯል /ሉቃ 1፥14/ ምክንያቱም ቅደስ ዮሐንስ የጌታ መንገድ ጠራጊ የአዋጅ ነጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ለብዙዎች ደስታ ምክንያት ከሆነ የድንግል ማርያም ልደት ምንኛ የሚያስደስት ይሆን፡፡ ስለሆነም ከጌታችን ቀን ቀጥሎ የምንደሰትበት ትልቁ ቀን የእርሷ የልደት ቀን ነው፡፡ የቀርጤሱ ቅዱስ እንድርያስ ስለ ከበረ ልደቷ እንዲህ ብሏል “ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምስሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌው በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነው፡፡” ብሏል፡፡ እመቤታችን ለፀሐዩ መምጣት የተዘረጋች ሰማይ፡ በቅድመ አያቶቿ በነቴክታና ጰጥሪቃ ህልም እንደታየችው በሌሊት የምታበራ ጨረቃ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጅ ሁሉ ደስታ ነው፡፡ ነቢያት በብዙ ሕብረ አምሳል የተናገሩላት “መሰረቶቿ የተቀደሱ ተራራዎች ናቸው” “ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች አበባዋም ከግንዱ ይወጣል” “ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ነይ” .ብለው ተናገሩላት ቅድስት ድንግል ማርያም ልደቷ የትንቢታቸው ፍፃሜ ነውና ታላቅ ደስታቸው ነው፡፡ /መዝ86፥1፤ ኢሳ 11፥1/ በዓለም ላይ የብዙ ታዋቂ ሰዎች ልደት ከሞቱም በኋላም ጭምር በታላቅ ድምቀት ይከበራል ታዋቂ ያልሆኑ ሰዎች ልደትም እንዲሁ ይታሰባል ለሰው ልጅ መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ምንኛ ሊከበር ይገባው ይሆን!
✝️✝️የግንቦት ልደታ በዓል አከባበር✝️✝️
በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት መሠረት ሃና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደው በአድባረ ሊባኖስ ሥር እመቤታችንን ወለዱ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸው “ንፍሮና ጥራጥሬ” ነበር፡፡ ይኼንን ትውፊት በመያዝ በዓሉ ከቤት ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ ሆኖም በበጎ ነገሮች ሰበብ ክፉ ዓላማውን ማስፈጸም የሚፈልገው ዲያብሎስ በማር መሃል መርዝን ከሚጨምርባቸው መንፈሳዊያት በዓላት አንዱ የግንቦት ልደታ የእመቤታችን በዓል ነው፡፡ አንዳንዶች በድፍረት ለአድባር ለዉጋር ነው፣ ቆሌውን ለመለመን ነው፣ እያሉ ንፍሮ የሚበትኑ፣ ቡና የሚረጩ፣ ቂቤ የሚቀቡ፣ የከብት ደም የሚያፈሱ፣ እነዚህ በእርግጥም ጣዖት አምላኪዎች ናቸው፡፡ እኛም ከእንደዚ ዓይነቶቹ አሰናካዮች በመለየት ይኼንን ታላቅ በዓል በተገባና በተረዳ ነገር እንድናከብረው የእመቤታችን ረድኤት በረከት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡ ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 1
መልዕክቱ ለሁሉም ይደርስ ዘንድ ሼር በማድረግ ያካፍሉ ጎዶልያስ ከፌስቡክ በተጨማሪ ቴሌግራም-https://t.me/rohobotorthodox ዩ ትዩብ- youtube.com/ጎዶልያስ ፌስቡክ- https://www.facebook.com/godolyass ላይ በመግባት ታገኟታላቹ አብረን እንማማርብታለን
Comments